የ3000 ዘመን ታሪክ ያላት ሁሌም ከአፋችን የማትጠፋው ኢትዮጵያ ማናት? እውነት ኢትዮጵያን እናውቃታለን? የማናቃትን ኢትዮጵያን መገንባት ይቻለን ይሆን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ስንሞክር ታሪክን የኋሊት ማየት ግድ ይለናል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀደምት የአለም ስልጣኔ አንዱ የሆነው የአክሱም ዘመነ መንግስት ጨምሮ በገናናነት የምትታወቅ ግዛቷ እስከ የመን ድረስ የነበረ በዘመናቱ እንደየ መልኩ ፍትሀዊ ፣ጀግና እንዲሁም ታሪክ ለዋጭ የሆኑ መንግስታት እና መሪዎች የተፈራረቁባት የነ አፄ ቴዎድሮስ፣ የነ ዩሀንስ፣ የነ ሚኒሊክን፣ የነ አብዲሳ አጋ፣ የነ አባኮስትር (በላይ ዘለቀ)፣ የነ ዶ/ር አብይ ሀገር መሆኗን ከብዙ በትንሹ ስለ ኢትዮጵያ ስናነብ የምናገኛቸው ታሪኮች ናቸው ፡፡ እኔ ዛሬ የምታቁትን የነ ቴዎድሮስ ታሪክ ለመናገር ሳይሆን አላማዬ ስለ ኢትዮጵያ ሲነሳ የነሱ ታሪክ እንዲነሳ ያስገደደውን ትክክለኛውን የኢትዮጵያዊነት እውነታ ማስረዳት ነው፡፡
ታሪካዊውን የአክሱምን ሐውልት ብናይ ኢትዮጵያዊያን ከአለት የፀና ወኔ ባለቤት የሆኑ መድከም እና ተስፋ መቁረጥ ስለማያውቁ ህዝቦች ይነግረናል ፡፡ የነ አፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ስናጠና ለጠላት እና ለውድቀት እጅ ከመስጠት ሞት እንደምንሻ ያስረዳናል ፡፡ የነ ዩሀንስን ታሪክ ብናይ እስከ መጨረሻ ድረስ ፀንቶ መቆምን ያስተምረናል፡፡ የሚኒሊክን ተጋድሎ ስንፈትሽ ህልምህ እና ነገህ ምንም ያህል ካንተ እና ከዛሬህ ቢገዝፉ መፍራትና መቆም ሳይሆን ችግርህን እና ፍርሀትን በመጋፈጥ ብሎም መስዋትነት በመክፈል ድልን መቀዳጀት መቻሉን ነው ፡፡ የነ በላይ ዘለቀን ታሪክ ብናስተውል ብትሸነፍ፣ ብትወድቅ እንኳን አንተ በቃ አበቃ ብለህ እስካልቆምክ ድረስ የመሸ ሌሊት ሁሉ መንጋቱ፣ የወደቀ መነሳት መቻሉ፣ የተሸነፈ መልሶ ማሸነፊያ እድል እንዳለው በተግባር የሚያሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በእነዚህ ኢትዮጵያዊ መነፅሮች ስናያት ማሸነፍ እንጂ መሸነፍ ምርጫ ያልሆነባት፣ ታጋሽ፣ ታጋይ፣ ፅኑ፣ ሩህሩህ፣ ፍቅር፣ ሰብአዊ፣ ብቃት እና ትጋት ማለት ናት ብለን መናገር እንችላለን ፡፡ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያን ምን እና ማን ሆና ነው፡፡ለጠላት እጅ ላለመስጠት ሀገር ለማዘመን ጥይት ለጠጣው የቴዎድሮስ ልጅ እንዴት ሀገር ክነዷ ሲዝል፣ እናት ስታነባ፣ ለድህነት እጅ ስንሰጥ ዝም ብሎ ሊያይ ይችላል? እንዴት የአብዲሳ አጋ ልጅ ሀገር ጩኸት ስትነጠቅ ኢትዮጵያ ታሪኳን ስታጣ ዝም ብሎ ያያል? ስለዚህ ኢትዮጵያን መገንባት ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ኢትዮጵያዊ መሆን ለፈለክ ተስፋ አለመቁረጥን፣ በችግሮች ውስጥ እልፎ ማሸነፍ የጠንካሮች (የኢትዮጵያዊያን) ምልክት መሆኑን ማቆም እና መሸነፍ ግን አማራጭ ሳይሆኑ የተሸናፊዎች ተምሳሌት መሆናቸውን፣ ለማሸነፍ መፈጠርህን እና ድል አድራጊነትን መቀዳጀት ይኖርብሀል፡፡
መድከም እና መዛል ከአላማ ፈቀቅ ለማለት በቂ ምክንያት ቢሆኑ ኖሮ አክሱም እና ላሊበላ ላይ የመጀመሪያውን መዶሻ ያሳረፈ እጆች ሁለተኛ ባልደገሙ ነበር ነገር ግን መሰናክሎች እና ችግሮች ውጣ ውረዶች ከአላማችን የሚያስቆሙን ሳይሆን ወደ አላማችን የሚያስፈነጥሩን ህዝቦች ነንና ታሪክ ተሸጋሪ ሃውልቶችን ዛሬም መቅረፅ እንችላለን። ስለሆነም ነገ ኢትዮጵያ እንድትለወጥ ዛሬ እኛ መለወጥ ይኖርብናል፣ ነገ ኢትዮጵያችን በልፅጋ እንድናያት ዛሬ እኛ እርስ በርሳችን መረዳዳት ይኖርብናል፣ እንድ ስንሆን ልዩነታችን ውበት ብቻ ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት የተሸሉ አማራጮችን ማያ በር የሚከፍት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን በችግር ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ዛሬን መስዕዋት አርገን ነገን ማዳን ነው። እሱ/እሷ ትላንት ይህን ማሳካት ችሏል/ችላለች እኔም ዛሬ ይህንን ማሳካት እችላለሁ የሚያስብል ታሪክን መስራት ነው ፡፡
በመሆኑም ፋሽስት ሆኖ የወረረንን ጠላት ድህነትን፣ ስንፍናን እና ፍርሀትን ለማጥፋት በእውነተኛ እና በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ዘራፍ ጎበዝ! ብለን መጀመሪያ እራሳችንን እና ስሜታችንን አሸንፈን እንዘምት ዘንድ ትላንት አባቶችህ በሞቱላት በገናናዋ ኢትዮጵያና በአኩሪው ኢትዮጵያዊነት ስም እጠይቃለሁ!
ጉዞ ወደ ለውጥ