ስለ ስምህና ስለዝናህ ከመጨነቅ ይልቅ ስለ ባህሪይ መጨነቅ ጀምር ፡፡ ስምህና ዝናህ የሚያመለክተው ሰዎች ስለ አንተ የሚያስቡትን ነገር ነው ፡፡ ባህሪይ የሚያመለክተው ግን ስለ እውነተኛ ማንነትህ ነው ፡፡ ስምና ዝና ምንጩ ሰው-ሰራሽ ነው ፡፡ ባህሪይ ምንጩ እውነተኛ ማንነት ነው ፡፡

እስከወዲያኛው የሚዘልቅን የውስጥ ሰላም ፣ መተማመንና እውነተኛ ስኬት የምታገኘው በባህሪህ ምክንያት ነው እንጂ ሰዎች ስለአንተ በሚያስቡት ነገር አይደለም ፡፡

ሰዎች ስለአንተ የሚያስቡት ነገር በየጊዜው ሊለዋወጥ ይችላል ፡፡ እውነተኛ ማንነተህ ግን ቋሚ ነው ፡፡ ሰዎች ስለአንተ የሚያስቡት ነገር በግል ልምምዳቸውና እይታቸው ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡ እውነተኛ ማንነተህ ግን ባለው እውነታ ላይ የተመሰረተ ነው ፡፡

ምንም እንኳን ለጊዜው ሰዎች ላይ ላዩን የተቀባ ሁኔታ አሳይተው ዝነኛ ቢሆኑም ፣ ይህ ላይ ላዩን የተለበጠው ቅብ ቀስ በቀስ እየደበዘዘ መሄዱ አይቀርም ፡፡ ያን ጊዜ እውነተኛ ማንነትን የያዘው ሰው እየደመቀ መሄዱ አይቀርም ፡፡

ላይ ላዩን የሆነው ሰው-ሰራሹ ይቅርብህና ውስጣዊው የሆነውና እውነተኛው ይሁንልህ!